Saturday, November 1, 2008

Attempt to Assassinate Amare Aregawe, Editor-in-Chief of the Reporter, Committed

Saturday, 01 November 2008
የሪፖርተር ዋና አዘጋጅ የግድያ ሙከራ ተደረገበት

ህክምና እየተከታተለ ነው

(በጋዜጣው ሪፖርተር)

የሪፖርተር የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጋዜጦች ባለቤትና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊ ዓርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ በድንገት ባልታወቁ አጥቂዎች በደረሰበት የግድያ ሙከራ ለጉዳት ተዳርጎ በሕክምና ላይ ይገኛል፡፡ ጤንነቱ እየተሻሻለ መሄዱን ተገል..ል፡፡

ዓርብ ጥቅምት 21/2001 ዓ.ም አማረ አረጋዊ እንደሌሎቹ የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረቦች ሁሉ ለዛሬ እሁድ በሚወጣው ጋዜጣ ሥራ ተጠምደዋል፡፡ የዕለት ሥራውን አጠናቅቆ የአባትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት ወደ ልጁ ትምህርት ቤት (አንድነት ኢንተርናሽናል ት/ቤት) ያመራል፡፡ ልጁን እቤት አድርሶ የወላጅ መምህራን ስብሰባ ስለነበረበት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ተገኝቶ ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ አገር ሰላም ብሎ ወደ መኪናው ሲያመራ አሸምቀው ሲጠብቁት በነበሩ ግለሰቦች ከኋላው ጭንቅላቱን ሲመታ ራሱን ስቶ መውደቁን በወቅቱ በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

አማረ ላይ ጥቃቱን የሰነዘረው ግለሰብ ግዳጁን ፈፅሞ እንዲያመልጥ የላዳ ታክሲ ቢዘጋጅለትም በታክሲው እንቅስቃሴ መታገድ ምክንያት በእግር ሮጦ ቢያመልጥም ግብረ አበሩ እንደሆነ የተገመተ አንድ ግለሰብና ባለታክሲው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፖሊስ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

በዕለቱ ጥቃቱ የተፈፀመበት ቦታ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለበት መሃል ቦሌ ከዲ.ኤች.ገዳ ሕንፃ ገባ ብሎ ካለው አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት 50 ሜትር ያህል አለፍ ብሎ የሚገኘው ማስክ ባር አካባቢ ነው፡፡

ጋዜጠኛ አማረ በግምት ከቀኑ 10፡30 ሰዓት ገደማ በጠራራ ፀሐይ ለመግደል በተመደቡ ሕገወጦች በቅርብ ርቀት ሆነው ባደረሱበት ድንገተኛ የድንጋይ ናዳ ራሱን ስቶ በወደቀበት በዚያች ደቂቃ በአንድነት ት/ቤት መምህርና ተረኛ የጥበቃ አባል ትብብር ለመጀመሪያ ዕርዳታ ወደ ሐያት ሆስፒታል ተወስዷል፡፡

በዕለቱ የሐያት ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች የደረሰበትን የጉዳት መጠን ለማወቅ የተሟላ ምርመራ ካደረጉ በኋላ በጋዜጠኛ አማረ ላይ የደረሰው ጉዳት ለክፉ የሚሰጥ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ ጥቃት ጀርባ እነማን አሉ?” የሚለውን ፖሊስ ጥቃቱ በአቶ አማረ ላይ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ በክትትል ላይ መሆኑንና በተያዙት ግለሰቦች መነሻነት ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የፖሊስ ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ጠቁመዋል፡፡

ጥቅምት 16/2001 በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ በአገር ደረጃ ስውር መንግሥታት አቋቁመው የፈለጉትን ለማድረግና ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውንና መንግሥት በጥሞና ሊያየውና ርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ተፅፎ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮ ቻናል ሳምንታዊ ጋዜጣ ለተከታታይ ሶስት ሳምንታት በአቶ አማረ ላይ ያነጣጠሩ ስም ማጥፋትና ማስጠንቀቂያ መሰል ፅሁፎች ሲወጡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ “የሪፖርተር ጋዜጣ የዛሬው ሁኔታ በእሳተ ጎመራ ላይ ከመደነስ የተለየ አይደለም፣ የሪፖርተር አባ አስገብር ጦር በአምስት ብርጌዶች የተደራጀ ነው እና ነብር ሆይ ጉድጓድ አትቆፍር..” በሚሉ ርዕሶች ዘለፋ ሲያወጣ ቆይቷል፡፡

ባለፈው አርብ በአቶ አማረ ላይ ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ ኢትዮ ቻናል በሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ላይ የፃፈውን ቀጣይ ፅሑፍ ወደማተሚያ ቤት ለሕትመት ካስገባ በኋላ ፅሑፉን መለወጡን ከሕትመት ክትትል ባለሙያዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

No comments: