Wednesday, July 2, 2008

አንዳንድ ነጥቦች ስለተቃውሞው ወገን


በጌታቸው ረዳ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ሀገራችን ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችን በሚመለከት የግሌን አስተያየት የሚገልፅ አንድ ፅሁፍ አቅርቤ ነበር።የነ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ‘አዲሱ የትግል ስትራተጂ’ እንደ መነሻ በመውሰድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ብዙም ሊበረክቱ ያልቻሉባቸውን መሠረታዊ ችግሮች ናቸው ያልኳቸውን የተወሰኑ ትዝብቶች ለማቅረብ ሞክሬ ነበር።በእኔ ግምት እንደዚህ ዓይነቱ ፅሁፍ ድርጅቶቹን በሚመለከት በስፋት የሚስተዋለውን በረባ ትንታኔ ላይ ያልተመሠረተ ድጋፍም ይሁን ተቃውሞን በቅጡ ለመፈተሽ የሚያስችል መጠነኛ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል ብየ አስቤ ነበር።ይሁንና አሁንም ቢሆን በጉዳዩ ላይ ስር የሰደደ የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዳሉ በትክክል ተረድቻለሁ። የፅሁፉ ዓላማ የተዳከሙ ድርጅቶች ጨርሶ ለማጥፋት የተሸረበ ሴራ ተደርጎ ተወስዶ ከሆነ ደግሞ፡ ዞሮ ዞሮ ተጠያቂው ተቃውሞ በፍፁም የማይፈቅደው የተቃውሞ ባህላችን እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል።ስለዚህ የአንዳንድ ሰዎችን ብዥታ በመጠኑም ቢሆን ያቃልል እንደሆን በማለት በርዕሱ ላይ የአሉኝን አስተያየቶች በዛሬው ፅሁፌም ዘርዘር አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ባለፈው ፅሁፌ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት በርካቶቹ የሀገራችን ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚስተዋሉባቸው እጅግ ብዙ ድክሞቶች ቢኖሩም በዛሬው ፅሁፌ በአራት ዋና ዋና ድክመቶቻቸው ላይ አተኩራለሁ።

የሀገራችን ተቃዋሚ ድርጅቶች አንዱ መሠረታዊ ችግር ወደ ተቀናቃኝ ድርጅትነት ማደግ አለመቻላቸው ነው። የሁለቱን ልዩነት በመጠኑም ቢሆን ላብራራ።ባለፈው ፅሁፌ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በአንድ ሀገር የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ የተቋቋሙ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱት ዲበአካላዊ(ሜታፊዚካል) ለሆነ ዓላማ አይደለም።ቢያንስ ቢያንስ ተቀናቃኝ ድርጅቶች የሚታገሉት ለሥልጣን ነው። ፓርቲዎች ዓለማቸው የፖለቲካ ሥልጣንን ህግ በሚፈቅደው አግባብ ለመያዝ እስከሆነ ድረስ ትግላቸው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወሳኝ መገለጫ መሆኑ እሙን ነው።ለዚህም ሲባል ተቀናቃኝ ድርጅቶች፡

 • በተለያዩ ያገሪቱ ክልሎች በሚኖሩ ህዝቦች ውስጥ በየደረጃው ዘልቀው በመግባት አባላትና ደጋፊዎችን ለማፍራት ይሠራሉ፤አባላት የሚመለምሉበትም መሥፈርት በግልፅ ያስቀምጣሉ።
 • ለዓላማዎቻቸው መሳካት ሲባል ይጠቅማሉ ያሏቸውን ግልፅ ስትራተጂዎችንና አቅጣጫዎችን በመተለም፡አስፈላጊውን ቁሳዊ፣ፖለቲካዊና ህሊናዊ ዝግጅት ያደርጋሉ።
 • ይነስም ይብዛም ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከሌሎች ተቀናቃኞች የሚለያቸውን የአጭርና የረዥም ጊዜ ፕሮግራማ ቀርፀው ይንቀሳቀሳሉ።
 • ምርጫ ተቃረበም አልተቃረበም ሀሳቦቻቸው ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያስችሏቸውን የቅስቀሳ ሥራዎችን ይሠራሉ።
 • የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ረዥም ጊዜን የሚወስድና የሁሉም ህዝቦች ዙርያ መለስ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ በማመን ለመተማመን ባህል መጎልበት የሚቻላቸውን ሁሉ ይሠራሉ።
 • ‘የመንግሥት ሥልጣን አሁንና እዚችው!’ በማለት አገር ይያዝልን አይሉም፤ ወዘተርፈ።

በአንፃሩ ደግሞ ባገራችን ውስጥ እስካሁን ተመስርተው ያየናቸው ድርጅቶች፣ ህብረቶች፣ቅንጅቶችና መድረኮች እንዳለመታደል ሆኖ እዚህ ግባ የሚባል የተቀናቃኝነት ቁመና ኖሯቸው ለማየት አልታደልንም።ሁሉም ማለት ይቻላል አገራችን ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ተቃዋሚዎች ብቻ ናቸው።

ተቃዋሚ ድርጅቶች ከተቀናቃኞች የሚለዩት፤

 • ልማድ ሆኖባቸው በዘፈቀደ ከሚጠሩት ግዙፍ ቁጥር በስተቀር በቅጡ የመዘገቧቸው ለቁጥር የሚገቡ አባላት የሏቸውም።
 • አባሉት አፈራን ባሉበት ወቅት እንኳ በግልፅ የሚታወቅ የምልመላ መሥፈርት በፍፁም አይኖራቸውም። ‘የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ’ አግኝተናል ብለው ስለሚያምኑ ‘ሁሉም ኢትዮጵያዊ አባላችን ነው!’ የሚል አስቸጋሪ ምላሽ ይቀናቸዋል።
 • ቀለል ባለ ምድራዊ ቋንቋ የሚገለፅ ለይስሙላም ቢሆን የተቀመጠ ፕሮግራም የላቸውም።
 • በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን በትንታኔ ላይ የተመሠረቱ ዝርዝር አቋሞችን ከመያዝ ይልቅ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥቅል መፈክሮችን ማሰማትን ይመርጣሉ።
 • የትግላቸው ዓላማ ‘ገዢውን ፓርቲ በመገርሰስ መሪዎቹን ለፍርድ ማቅረብ’ እንደሆነ ስለሚያውጁ ወዳጅ ተጠላት ሁሉንም ያስበረግጋሉ።
 • በየእንጀራቸው ተሠማርተው ይከርሙና “ገዢው ፓርቲ በሩን ገርበብ እንዳረገው” በመገንዘብ በምርጫ ሰሞን በመሰባሰብ “በርግደው ለመግባት” ለሥልጣን ያበቃናል ያሉትን ያለ የሌለ መንገድ ለመጠቀም ይሞክራሉ።
 • ባጭሩ በተቃውሞ ተወልደው፤ በተቃውሞ ጀንበር ታዘቀዝቅባቸዋለች።

ያገራችን ተቃዋሚ ድርጅቶች ሌላው ችግር፡ በተናጠል የሚደራጁበትም ሆነ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ህብረት የሚፈጥሩበት በይፋ የሚታወቅ ንዑስ ፕሮግራም ኖራቸው የማያውቅ መሆኑ ነው። ምናልባትም ደግሞ ያስፈልገናል ብለው አያምኑም።በርካታ ትብብሮች አስራ ምናምን ጊዜ ተቋቁመው፣ አስራ ምናምን ጊዜ ፈርሰው ሲያበቁ፡ እንደገና ባዲስ መልክ በሌላ ዙር ዘመቻ ለማገገምና እግር ለመትከል ሲራኮቱ፡ ለጉድ ጎልቶን እያየናቸው አልፈዋል። በርካታ ያልተሳኩ ጥረቶችና ያልተጨበጡ ህልሞች እያየን እዚህ ደርሰናል። ይህን መሠሉ የተቃዋሚዎቻችን የማያቋርጥ የዘወትር ሽክርክሪት በማያሻማ መልኩ የሚነግረን ከላይ የጠቀስኩትን ይኸን አሳዛኝ እውነታ ነው። ከ1984 ዓ.ም. ወዲህ ባገራችን የፖለቲካ መድረክ ተፈጥረው ለረባ ፍሬ ሳይበቁ የከሠሙ ስንት አማራጭ ምክርቤቶች፣ስንት ህብረቶች፣ስንት ቅንጅቶችና ስንት መድረኮችን እንደታደምን ቤቱ ብቻ ይቁጠረው።

የፕሮፌሰር በየነ አማራጭ ሃይሎች ምክርቤት/ኢዴሃቅ/ህብረት( አሁን ደግሞ መድረክ!) ውስጥ ተካተው የነበሩትም ሆነ አሁንም ድረስ ያሉት ‘ሃይሎች’ ያላቸውን ለእስከወዲያኛው የማይታረቅ ጠላትነት ላወቀ፡ ምን ንዑስ ፖለቲካዊ ፕሮግራም አንድ ላይ እንዳሰባሰባቸው ለመረዳት ራሱን የቻለ ሳይንስ ሳይጠይቅ አይቀርም።ኢህአፓና መኢሦን፣ ኢዲዩና ዓረና ትግራይ፣ አቶ ስየ አብርሃና ቀኛዝማች ነቅዓ ጥበብ፣ ዶ/ር ነጋሶና ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ ወዘተርፈ፤ ሊጋሩት የሚችሉትና ‘ፅኑ የትግል ጓዶች’ ለመሆን የሚያበቃቸው የፖለቲካ አቋም ምን እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻል አይመስለኝም።

ሌላውን ሁሉ ትተን ከአሥራ ስንት ዓመታት በሗላ እንደ መዳፋችን አብጠርጥረን የምናውቃቸው የሚመስሉን ፕ/ር በየነና ዶ/ር መረራን ለምሣሌ እንውሰድ።ህብረታቸው ወይም አዲሱ መድረክ በሆነ አጋጣሚ የፖለቲካ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በቃ እንበል። የዶ/ር መረራ ጉዲና ኦብኮ/ኦህኮ “ለምለሙ የኦሮሚያ መሬት ተመልሦ በነፍጠኛው እጅ እንዳይገባ” ሲባል በመንግሥት እጅ መሆን እንዳለበት በፅኑ ያምናል። የፕ/ር በየነ የሀዲያ ህዝብ ግንባር/ደቡብ ህብረት/ኢሶዴፓ በበኩሉ፡ “የገበያ ህግ በሚደነግገው መሠረት መሬት መሸጥ መለወጥ” እንዳለበት አጥብቆ ይሟገታል። ልዩነትን ተቀብሎ የመሄድ ባህል በሌለበት ሀገር እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ አዎንታዊ ሊመስል ይችል ይሆናል። የ ‘መቻቻላቸው’ ምክንያት ግን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ እንዲኖር ከምንመኘው የመቻቻል ባህል ጋር ያለው ቁርኝት እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ብዙም ነቃሽ የሚያሻው አይመስለኝም።

ዶ/ር ብርሃኑና ኢ/ር ሃይሉ ሻውል የቀድሞ ድርጅታቸው ቅንጅት የሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም በሚመለከት ከእውነትነት ይልቅ ወደተረትነት የቀረበ ልግሥና ነበራቸው። ‘ሊበራል ዴሞክራሲ’ ምን እንደሆነ ሊያብራሩልን ብዙም ግድ ያልነበራቸው ቢሆንም፡ ሃይማኖታቸው እስኪመስለን ድረስ በተገኘው መድረክ ሁሉ ሲሰብኩልን ነበረ።በወቅቱ ለጋዜጦች ይሰጧቸው ከነበሩት ቃለ መጠይቆች በተደጋጋሚ ለመረዳት እንደቻልነው፡ ቅንጅታቸው በርካታ ሥራዎችን የመሥራት እቅድ ነበረው። በወቅቱ በተነገረው መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ የሚዘረጋ የህዝብ ማመለላሻ ባቡር አገልግሎት መጀመር ከዕቅዶቻቸው አንዱ እንደነበር ሰምተናል።በወቅቱ ግን ከመሪዎቹም ሆነ ከደጋፊዎቻቸው መሃል ‘የባቡሩ ፕሮጀክት’ በባህሪው ወደሶሻሊስትነት በጣም የሚያደላ ከመሆኑ የተነሳ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንኳ እስከዚህም ደፍሮ የማይገባበት እንደሆነ የጠቆመ አልነበረም።

የፕ/ር መስፍን ‘ሶሻሊስት ዴሞክራትነት’ ከኢንጅነር ሃይሉ ‘ሊበራል ዴሞክራሲ’ ይልቅ፡ ‘ያገዛዝ ሥርዓቱ’ ለሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተሻለ ቅርበት አለው ብሎ መሞገት ይቻላል።ዶ/ር ብርሃኑ በ ‘አዲሱ ስትራተጂያቸው በሁለ-ገብ ትግል ሊገረሥሱት’ የተነሡት ‘የአቶ መለሥን የጎሳ ፖለቲካ’ እንደሆነ ቋቅ እስኪለን እየሰማን ነው። ይሁንና ይኸኛው አቋማቸው ኢትዮጵያን ‘በጎሳ ለመገነጣጠል’ ነፍጥ ካነገቡ ነውጠኞች ጋር ቺርስ ከመባባል ፈፅሞ ሊያግዳቸው አይችልም። አቶ ገብሩ አስራት ወደ ‘ዴሞክራሲያውያን ሃይሎች’ ጎራ ለመቀላቀል፡ዝርዝር አቋማቸውን ማሳወቅ አላስፈለጋቸውም፡፡ ላለፈ ጥፋታቸው (በአሰብ ጉዳይ?!) ባደባባይ ይቅርታ መጠየቅ መቻላቸው ብቻ በቂ ነበረ።(ምንም እንኳ በብዙዎች ዘንድ ያለፈ የትግል ታሪካቸውን ሙሉ በሙሉ እንደባከነ መቁጠራቸው ባይወደድላቸውም!)

በቅርቡ እንደሰማነው ደግሞ አቶ ስየ አብርሃ ከ ‘ዕብሪተኛ የወያኔ መሪዎች’ ዝርዝር ወጥተው ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ለውጥ አራማጅነትና ‘በሳል ፖለቲከኝነት’ ጎራ መመደብ የቻሉበት አስገራሚ ሽግግር እንዳደረጉ ተነግሮናል።ማንኛችንም ለማየት እንደቻልነው የአቶ ‘ሽግግር’ ረዘም ያለ የሃሳብ ልውውጥም ሆነ መሠረታዊ የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ለመፍጠር የሚያስችል መድረክ የጠየቀ አልነበረም። የተቃውሞውን ጎራ ለመቀላቀል የሚያስፈልገው ብቸኛ የይለፍ ቃል፡ “የመለሥ አምባገነን አገዛዝ ላለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት” የፈፀማቸውን ተግባራት ዓይንን ሳያሹ መኮነን ብቻ ነው።

ዝርዝሩን ገልፀን የምንጨርሰው ስለማይሆን በዚሁ እንለፈውና፡ የአንድ ሚልየኑን ብር ጥያቄ እናንሳ። እነዚህ ሁሉ ህልቆ መሣፍርት የሌላቸው ባተሌ ተቃዋሚዎች ባንድ ቅንጅት፣ባንድ ህብረትም ሆነ ባንድ መድረክ ለመሰባሰብ ያበቃቸው የሚታወቅ የጋራ መስመር ወይም ርዕዮት በእርግጥ አላቸውን?! ከግራም መጡ ከቀኝ ተቃዋሚዎቻችንን አንድ ላይ እንዲያብሩ የሚያደርጋቸው የጋራ ፕሮግራምም ሆነ የሚታወቅ መርህ-ተከል ርዕዮት የላቸውም፤ ወይም ደግሞ በፍፁም አያስፈልጋቸውም። ሃገራችን ለገጠሟትም ሆነ ወደፊት ለሚገጥሟት ችግሮች ምክንያቱም ሆነ መንስዔው አቶ መለሥ መሆናቸውን መቀበል ብቻ በቂ ነው። ይኸ ደግሞ መቀባባቱን ትተን በትክክለኛ ሥሙ እንጥራው ከተባለ ንፁህ ጥላቻ ብቻ ነው። ከዚህ መሰሉ የጋራ ጥላቻ ውጭ እስካሁን ያየናቸው ህብረቶች፣ቅንጅቶች፣አንድነቶችም ሆኑ መድረኮች፡ ተቻችለው ለአንዲት ጀንበርም ብትሆን መዝለቅ ቢችሉ እንኳ ራሱን የቻለ ተዓምር ነው!

የተቃዋሚዎች ሌላው ችግር ምድራዊ መመዘኛ በሌላቸው ሰማያዊ ፅንሰ ሃሳቦች ተጠፍረው የሚንከላወሱ መሆናቸው ነው።ዓላማዎቻችን የሚሏቸው ነገሮች ከሚጨበጡ ግቦች ይልቅ ዲበአካላዊ ቅኝት(ሜታፊዚካል ሪዞናንስ) ያመዘነባቸው ፅንሠ ሃሳቦችን መጥቀስ ያበዛሉ።የመደራጀታቸውን ወይም በህብረት የመቀጠላቸውን አስፈላጊነት በተመለከተ የሚሰጧቸው ብዙዎቹ ገለፃዎች የባህታውያንና የነቢያት ብቻ ይመስሉን በነበሩ አስፈሪ ቃላትና ሃረጎች የሚሞሉበት ጊዜ ያመዝናል። የሚቋቋሙበትም ሆነ ከሌሎች ጋር ህብረት ለመፍጠር የሚያስቡበት ምክንያት፡ከዕለት ተዕለት ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ጋር ከማስተሣሰር ይልቅ፡ “ትውልድን ከእልቂትና ከመከራ ማዳን” በሚሉና በሌሎች መሠል ቋንቋዎች የሚገለፅ ‘መሢሃዊ’ ተልዕኮ ማነገብን ይመርጣሉ። የምፅአት ወሬና የአርማጌዲዮን መቃረብ ዜና ካላከሉበት ህብረታቸው የሚሰነብት አይመሥላቸውም። “ይህች አገር የገባችበት የጥፋት ማጥ፣ ወደ ገደል የሚገባው ባቡር፣ የጎሳዎች የእርስ በርስ መባላት” ወዘተ ብለው ካላስፈራሩን ተቃውሟቸው ድምቀት የማይኖው ይመሥል በስምንተኛው ሺህ ወሬ ያዋክቡናል።

ከተቋቋመ ጀምሮ የርስበርስ ጭቅጭቅ ተለየቶት የማያውቅ፣ አለመተማመን የነገሠበት፣ ወዴት መሄድ እንዳለባቸው በቅጡ በማያውቁ አመራሮቹ አለመግባባት ህልውናው ቋፍ ላይ የደረሰን ድርጅት እንዴት ሦስት ዓመት ሙሉ ሥራ አስፈትቶን እንደከረመ የምንስተው አይመሥለኝም። መሬት ላይ የቆመ እግር ያልተከለን ድርጅት ‘ቅንጅት መንፈስ ነው!’ የሚል ሰማያዊ ተልዕኮ አሸክሞ (ቀድሞውኑም ባልነበረው አቅም!) ከተፈጥሮአዊ ዕድሜው በላይ እንዲቀጥል የተደረገው ከንቱ ልፋት የትም ሊደርስ ያልቻለውም ለዚህ ነው።ባመራሩ ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠርም ሆነ ከውስጥ ድክመት የመነጨ ከበድ ያለ የህልውና ፈተና ሲገጥም፡ ቀበቶን አጥብቆ በውይይትና በአመራር ብቃት፤ ወይም በህዝብ አመኔታ ላይ በመመሥረት መፍትሄ መሻት ብዙም አይታሰብም። ይልቁንም “የኢትዮጵያ ህዝብ ተዓምር መፍጠር አያቅተውም፤ አንዳች ተዓምር ተፈጥሮም ቢሆን” ወዘተርፈ ወደሚሉ መጨበጫ የሌላቸው ኢ-ፖለቲካዊ (መንፈሳዊ) ማፅናኛዎች መጠጋትን ይመርጣሉ።

ተቃዋሚዎቻችን የተጠናወታቸው ሰማያዊነትን/መለኮትን የሚታከክ አባዜ፡ ራሳቸውን የድርጅት ጥንካሬ፣የዓላማ ፅናት፣የመስመር ጥራት ወዘተ በመሳሰሉት የሚታዩ መሥፈርቶች በመመዘንና በመፈተሽ አካሄድን ለመቃኘት ከመሞከር ይልቅ፡ ጊዜን በጉንጭ አልፋ ክርክር እንዲያሳልፉ ዳርጓቸው አስተውለናል።አሁን አሁን ‘ቅንጅት’ን ያቋቋሙት ሃይሎች ወደ አሥራ ምናምን ትንንሽ ተበታትነው እያለ ጭምር፡ “የመንፈሱ ወራሾች እኛ ነን” የሚል አስቂኝ ሙግት ውስጥ ገብተው የምናየውም ለዚህ ነው። መፍትሄው ከሰማያዊ ይልቅ ምድራዊነቱ ወዳመዘነ የተቀናቃኞች ፖለቲካ ውለው ሳያድሩ መመለስ መቻል ነው።

በመጨረሻ ላነሳው የምፈልገው የተቃዋሚዎቻችን ድክመት ደግሞ ባለፈው ፅሁፌ ማጠቃላያ ላይ ላነሳው የሞከርኩት ነጥብ ነው። አሁንም ቢሆን የብዙዎቹ ችግር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ፈፅሞ የማያውቁ መሆናቸው፤ ወይም ደግሞ ለማወቅ አለመዘጋጀታቸው ነው። ይኸንን እውነታ ከማንም በላይ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ባንድ ወቅት ‘ርዕይ 2020’ በተባለ መድረክ ላይ በ1996 ዓ.ም. ባቀረቡትን ፅሁፍ በትክክል አስቀምጠውት እንደነበር አስታውሳለሁ። አቶ ደሳለኝ ራህመቶ የዮሃንስ ራዕይ ጥላ ያጠላበት(አፖካሊፕቲክ) ይመሥላል በሚል በገለፁት በዚህ ፅሁፍ ውስጥ በርካታ ጉዳዮችን ተነስተዋል። ፕ/ሩ በኢህአዴግ ‘ያገዛዝ ሥርዓት’ ፖሊሲዎች አማካይነት ኢትዮጵያ የጥፋት ገደል አፋፍ ላይ እንደደረሰች ይገልፃሉ።አገሪቱ ከጥፋት የምትድንበት ብቸኛ ዕድል ኢህአዴግ በቀጣዩ ዓመት(ምርጫ 97!) ለተቃዋሚዎች ሥልጣኑን አሳልፎ የሰጠ እንደሆነም ተንብየው ነበር። እንደሳቸው እምነት “የሚያውቋት ኢትዮጵያ ከመሠረቷ እንደተናደች” ና ይደርሳል ብለው የተነበዩት የመጨረሻ ምዕራፍ በ1997 ክረምት ላይ እንደሚገባ ባፅንኦት ሞግተዋል። 97 ክረምትን ለምን የመጨረሻው ምዕራፍ መባቻ መሆኑን የገለፁበት ዋነኛው ምክንያት በኢህአዴግ “መርዛም አስተሳሰብ ተኮትኩቶ ያደገው” ያሉት ትውልድ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የሚጀምርበት ጊዜ በመሆኑ እንደሆነ ይጠቁማል ፅሁፋቸው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ፕሮፌሰር መስፍን የሚያውቋት “ከመሠረቷ የተናደችው”ን ኢትዮጵያ የተካችዋ ኢትዮጵያ ስትሆን፤የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲሶቹ ዜጎች ደግሞ ፕ/ሩ የጥፋት ወኪሎች እንደሚሆኑ የገመቷቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ70% የማያንስ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ናቸው። ተቃዋሚዎች ይኸን እውነታ ለመቀበል ካልደፈሩ የፖለቲካው ዓለም ዳይኖሰሮች ሆነው የሚቀሩበት ዕድል እጅግ ከፍተኛ ነው።

No comments: