Pages

Friday, July 25, 2008

ምዕራቡ ዓለምና የዴሞክራሲ ሬቶሪክ

ጌታቸው ረዳ

ከጥቂት ወራት በፊት በዚምባብዌ የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ የምእራባውያን የዜና ማዕከላት ትኩረት በሮበርት ሙጋቤ እጣና በአፍሪካ አህጉር የዴሞክራሲ ሂደት ላይ አድርገዋል።የአፍሪካ ህብረት በሻረም አል ሼክ ተሰብስቦ በመከረበት ወቅት የዚምባቡዌና የሙጋቤ ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ነበረ።በጃፓን በተካሄደው የቡድን ስምንት ሀገራት ስብሰባ ላይም እንዲሁ ተመሳሳይ ጩኸት ተስተጋብቷል።በእኔ ዕምነት በጉዳዩ ላይ የምዕራቡ ዓለም መንግስታትም ሆኑ የመገናኛ ብዙሃን እያደረጉት ያሉት የተጠናከረ ዘመቻ የዚምባቡዌና የሙጋቤን ብቻ ሳይሆን አህጉሪቱ ለወደፊት የሚገጥሟትን ፈተናዎች ጭምር አመላካች ነው።ከላይ በጠቀስኳቸው ሁለት መድረኮች ላይ የአፍሪካ መሪዎች በሙጋቤ ላይ አሳዩት የተባለው ለስለስ ያለ አቋምም ይኸንን ፈተና በትክክል ከመገንዘብ የሚመነጭ ይመስለኛል።

ምዕራቡ ዓለምና የዴሞክራሲ ሬቶሪክ

እንግሊዛዊው ገጣሚ ራድያርድ ኪፕሊንግ በህይወት ዘመኑ ከሠራቸው የጥበብ ሥራዎች መካከል፡ ‘ዘ ዋይት ማንስ በርደን’ የሚል ርዕስ የሰጠው አሪፍ ግጥም ይገኝበታል።

Take up the White Man's burden--
Send forth the best ye breed--
Go bind your sons to exile
To serve your captives' need;
To wait in heavy harness,
On fluttered folk and wild--
Your new-caught, sullen peoples,
Half-devil and half-child.

By open speech and simple,
An hundred times made plain
To seek another's profit,
And work another's gain.


በየደረስክበት ሁሉ፣

እንጭጭ አንጎል ያላቸው ከጋኔን አብራክ ‘ሚከፈሉ፣

ከሰውነት ተራ የወጡ ወደ ዱር አውሬነት ያደሉ

በፍርሃት መረብ ተሸብበው ሰርክ በሽብር የሚኖሩ፣

አህዛብ ገብተዋል በእጅህ ያንተን ደግነት የሚሹ።

ዓለም በግልፅ ይወቀው

ራስህን ሳታስቀድም የአውሬዎቹን ጥቅም ብቻ አስበህ፣

በፅኑ ሰንሰለት ጠፍረህ ፣

ወደ መልካም መስክ ማሰማራት ያንተ እዳ መሆኑን አውቀህ፣

የስደትን አበሳ አስተምርና ምርጥ ልጆችህን አሰማራ፣

እንዲሸከሙ የነጮቹን ፈተና።

ኪፕሊንግ በዚህ ግጥም ምዕራቡ ዓለም ‘ያልሰለጠነውን’ ዓለም ከጨለማ የማውጣትን መለኮታዊ አደራ ጫንቃው ላይ እንደተሸከመ ዓለምን ሊያሳምን ሞክሯል።የታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛት የማስፋፋት ዘመቻ አካል እንደነበር ይነግረናል ባለቅኔው።

ዛሬ ከመቶ ዓመታት በሗላ ደግሞ፡ ናታን ሻራንስኪና ፍራንሲስ ፉኩያማን የመሳሰሉ የምዕራቡ ዓለም ሊቀ መኳሶች፡ ምዕራባውያን ‘ያልሰለጠነውን’ ዓለም በዴሞክራሲያዊነት ፀበል የማጥመቅ ታሪካዊ/‘መለኮታዊ’ ሃላፊነት እንዳለባቸው፤እንዲሁም መላው ዓለም ከዚህ ጥምቀት በተዓምር እንደማያመልጥ ቢገነዘበው እንደሚበጀው እየነገሩን ይገኛሉ።

በአፍሪካና በሌሎችም በልማት ወደ ሗላ የቀሩ ሀገራት ላይ የነበራቸው ተፅእኖ ለዘመናት ለማዝለቅ የቻሉት እንደየዓለማዊ ሁኔታው/እንደየአስፈላጊነቱ አካሄዳቸውንና ፍልስፍናዎቻቸውን በመቀያየር ነው። በቅኝ አገዛዝ ዘመናት ያለሃፍረት ዓይን ያወጣ ዘረፋ ላይ ተሰማርተው መዛቅ የቻሉትን ሁሉ ሲዝቁ ኖረዋል። ከነበራቸው የጠመንጃ የበላይነት በተጨማሪ የነራድያርድ ኪፕሊንግ ርዕየተ ዓለማዊ ድጋፍና የነአባ ማስያስ ወንጌላዊ መልዕክት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። ከ1960ዎቹ ወዲህ እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ድረስ በእጅ አዙርና በአሻንጉሊት አስተዳዳሪዎች እየታገዙ መቀጠል ችለው አይተናል።ፒኖሼ፣ሱሃርቶ፣ሞቡቱ ናትሩሂዮን የመሣሠሉት ‘የብረት መዝጊያ’ የሆኑ ደንበኞች ስለነበሯቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ከማግኘት የሚከለክላቸው አልነበረም። ከነዚህ መሪዎች ጋር ያደርጉት የነበረውን ‘ትብብር’ የሚያቀጣጥለው ሞተር ደግሞ ‘የኮሚኒዝምን መስፋፋትና የዶሚኖዎቹን ተከታትሎ መውደቅ’ ለማስቀረት ይደረግ የነበረው ዘመቻ ነበር።

የኮሚዩኒዝም ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካከተመባቸው ከአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ወዲህ ደግሞ፡ የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም(ሳፕ)፤ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ግንባታ አጀንዳን (ጉድ ጋቨርናንስ ዲስኮርስ) ለዘመናት የዘለቀውን የኒዮ ሊበራሊዝም ተፅእኖ ለእስከወዲያኛው ለማስቀጠል ሲባል ጥቅም ላይ የዋሉና በመዋል ላይ የሚገኙ ሥልቶች ናቸው። ከሁሉም ምዕራባውያን አንደበት የማይጠፋው መሪ ሃረግ(ካች ፍሬዝ) ግን “ዴሞክራሲን የማስፋፋት” ተልዕኮ ነው።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብቷል ለመባል መድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣‘ነፃ ምርጫ’፣ ፕራይቬታይዜሽን፣የንግድ ሊበራላይዜሽን፣ ‘ነፃ’ ፕሬስ፣የሲቪክ ማህበራት(መያዶች) ወዘተርፈ በአንድ ሀገር መሟላት ካለባቸው ግዴታዎች የተወሰነቱ ናቸው።ይኸ መሆኑ በርግጥ ባልከፋ።እንዳጋጣሚ ሆኖ የምንናገረው እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት(ነዳጅ፣ወርቅ፣መዳብ) ስላለው ሀገር ከሆነ እላይ የጠቀስናቸው ተቋማት እምብዛም ላያስፈልጉ ይችላሉ።ጥያቄዎቹ እንዲሁ ለግብር ይውጣ ሊጠየቁ የሚችልበት እድል ግን ይኖራል።በኒዮ ሊበራል አጀንዳ አራማጅ ምዕራባውያን ዘንድ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሥልጣን ላይ ያሉ መንግስታት ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አድርገዋል ሊባሉ የሚችሉት የተደረገው ምርጫ እነርሱ ትክክለኛ ነው ብለው ያቀረቡትን አካሄድ ብቻ ተከትሎ የተደረገ እንደሆነ ነው። ምርጫ የሚደረገው የነሱን ውቃቤ ለማስደሰት ሲባል ብቻ እንደሆነ ስለሚያምኑ አንድ አንድ ጊዜ አገሬው በነቂስ ወጥቶ ቢመርጥም ደስ ካላላቸው ዴሞክራሲያዊነቱን ባንድ መግለጫ ብቻ ሊሽሩት ይችላሉ።ለምሳሌ ኡጎ ቻቬዝ ወርዶ እስኪያዩት ድረስ ቬኔዝዋላ ውስጥ መቼም ዴሞክራሲ ተረጋግጧል የሚባል ጨዋታ ሊዋጥላቸው አይችልም።

ስልጣን በፉክክር ለመያዝ አስበው የሚንቀሳቀሱ ተቀናቃኝ ድርጅቶች ለዴሞክራሲ ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ብዙም ሙግት የሚያስፈልገው አይመስለኝም። የምዕራባውያኑ የዲሞክራሲ ተዋስኦ የሚያቀነቅነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ለራስ ሀገርና ህዝብ ሊኖር ከሚገባው ታላቅ ሃላፊነት የግድ መቆራኘት አይጠበቅበትም።ታዋቂ ሰው የሚመራውና ለትልቅ ለትንሹ አጋጣሚ ሁሉ ወደየ ሃብታም አገራት ኤምባሲ መሮጥ የሚቀናው ስብስብ ሁሉ አባላት መለመለም አልመለመለም የዲሞክራሲያዊ ሂደቱ አንደኛ ዘዋሪ ተደርጎ በየዕለቱ መሞካሸት ይጀምራል።አንዱን ጎሳ በሌላው ላይ አነሳስቶ ግርግር መፍጠር ከቻለየስልጣን መጋራትካልተደረገ ምፅዓት ይመጣል ብሎ የሚያስቸግር ዓይና አውጣ ሆኖ ያርፈዋል።ራሽያ ውስጥ ጋሪ ካስፓሮቭ የሚባል ዝነኛ ቼስ ተጫዋች የራሽያን ህዝብ ከመከራና ከነፑቲን አምባገነን አገዛዝ የማውጣት ተልዕኮ የያዘ ፓርቲ በማቋቋሙ ብቻ በምዕራባውያን ዘንድ እንደ ራሽያ የወደፊት ተስፋ ሊቆጠር በቅቷል።ለተራ አጀብ እንኳ የሚሆን የረባ ተከታይ አለማግኘቱ ለምዕራባውያኑ ምንም ማለት ላይሆን ይችላል። ደጋፊዎች አፈራም አላፈራም ካስፓሮቭ የራሽያ ዲሞክራሲ ተቀልብሷል ማለት መቻሉ ብቻ ይበቃል።ለነገሩ ምዕራባውያኑ ዓመል ሆኖባቸው ራሽያ ላይ ያፈጣሉንጂ አፍሪካ ውስጥ ያላቸውን ተፅዕኖ አንድ ሚልየንኛም ብትሆን ሊኖራቸው አይችልም።

የምዕራባውያኑ የዴሞከራሲ ሬቶሪክ ከተቃዋሚዎች ተሳትፎ አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መግፋት የጀመሩትመፍትሄምአለ። የስልጣን መጋራት(ፓወር ሼሪንግ ዲል) ይባላል።የዚህ ሃሳብ ትክክለኘነት የሚመነጨው ምዕራባውያኑ ላላቸው ጥቅም ተገቢ ሆኖ ያገኙትን ሃሳብ ሁሉዲሞክራሲያዊነትለማላበስ ካላቸው መብት ብቻ ነው።ደጋፊዎቼ ተቆጥተዋልና ስልጣን ካልተጋራሁ ሞቼ እገኛለሁ!” የሚል አምታች ሁሉ የዴሞክራሲያ ሂደቱ መጠናከር ወሳኝ ሃይል ሆኖ ይወደሳል። እነሆ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የፀደቀ ህገ መንግስት በዝርፊያ በተጣሉ ሁለት ወመኔ ፖለቲከኞች ፊርማ የሚሰረዝበትዲሞክራሲየምናይበት አስገራሚ ሰዓት ላይ ደርሰናል።

ኬንያን ለአብነት እንጥቀስ። ራይላ ኦዲንጋ በርካታ ደጋፊዎች መርጠውት ሊሆን ይችላል።ምርጫው ሊጭበረበርም ላይጭበረበርም ይችላል።ምዕራባውያኑ (ኮፊ አናን የድራማው መሪ መሆናቸው ለውጥ የለውም!) የኬንያውያንን የእርስ በርስ መተላለቅ ለማስቀረት በማሰብ የስልጣን መጋራት ሃሳብ መግፋት እስኪጀምሩ ድረስ የኦዲንጋ አቋም ምርጫው ስለተጭበረበረ መደገም አለበት የሚል ነበረ። በፀጥታ ሃይሎች የተገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ጉዳይ ይጣራ እያለ ሲጮኽ ሰምተናል።ይሁንና በምዕራባውያኑምክርመሠረት ድሆች ወገኖቹ ዝር በማይሉበት የጎልፍ ሜዳ ውስጥ ተቀምጦ ደመኛ ጠላቱከኪባኪ ጋር ስልጣን ለመጋራት ከመስማማት አላገደውም።የሞቱት ካንድ ሺህ የሚበልጡ ሲቪሎች ጉዳይ ከዚያ በሗላ ማንሳት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃውንዲሞክራሲአደጋ ላይ ስለሚጥልበት የሚሞክረው አይሆንም። ይባስ ብሎ በዚምባብዌ ስለተካሄደው ምርጫ ከተሰጡት አስተያየቶች ሁሉ አስገራሚውን ውግዘት ያቀረበው/ሚኒስትርኦዲንጋ ነበር። ሰውየው ለሲኤንኤን የሰጠው አስተያየት ሙጋቤ ኢዝ ዲስግሬስ ፎር አፍሪካ!” የሚል ነበር።ኦዲንጋ የምሩን ይሁን የቀልዱን ለማወቅ ባይቻልም፡ አፍሪካ ህብረት በዚምባቡዌ ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈፀም እንደሚገባው ለማሳሰብ ጭምር ሞክሯል።

በምዕራባውያኑ ተዋስኦ መሠረት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትየግድ ከሚላቸውተቋማት ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች(መያዶች) ያላቸው ሚና ትልቅ መሆኑ በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ መግባት አይኖርበትም። የአገር በቀል መያዶች የህዝብን ዙርያ መለስ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ በማነሳሳት ረገድ ያላቸው ሚና በፍፁም የሚካድ አይደለም። ነገርግን የድርጅቶቹ ተጠያቂነት ድርጎ ለሚሰፍሩላቸው ምዕራባውያንቀጭን ጌቶችብቻ በሆነበት እውነታ ውስጥ፡ የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ በሌሎች ላይ ጥበብለመጫን የሚያስቡ ባዕዳን መጠቀሚአ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል።በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ መያዶች ተጠያቂነታቸው እናገለግለዋለን ለሚሉት ሃገርና ህዝብ መሆኑ የሚቀርበት ሁኔታ(ኤክስተርናላይዜሽን ኦፍ አካውንቴቢሊቲ) ይፈጠራል።ሪታ አብራምሰንዲሲፕሊኒንግ ዴሞክራሲበሚል ርዕስ በሰጠችው መፅሃፏ ላይ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ትንታኔን አቅርባለች። በእርግጥም ሪታ በትክክል እንዳስቀመጠችው፡ይኸው የመያዶች ገፅታ ከምንም ነገር በላይ አፍሪካ ውስጥ በተደጋጋሚ ለሚስተዋሉ የፖለቲካ ብጥብጦች በዋና እርሾነት ያገለገለበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።

በምዕራባውያኑ የመልካም አስተዳደር ተዋስኦ መሠረት ማንኛውም አፍሪካ ውስጥ በግል ሚድያነትም ሆነ በመያድነት የተቋቋሙ አካላት ሁሉ በተፈጥሮአቸው ዴሞክራቲክ (ኢንኸረንትሊ ዴሞክራቲክ) ተደርገው የሚወሰዱበት ስነ ሞገት በበርካታዎቹ ሀገራት ማህበረ-ፖለቲካዊ መቼት ውስጥ ያለውን እውነታ በፍፁም ያገናዘበ አይደለም። ባንድ ሀገር ውስጥ ያሉ መያዶች አደረጃጀትም ሆነ እንቅስቃሴ የሚገዛበት ስነልቦናና አወቃቀር ዞሮ ዞሮ በሚፈጠሩበት ማህበረሰብም ሆነ ቡድን ውስጥ በስፋት የሚስተዋለውን እውነታ መከተሉ የማይቀር ነው። በመደብ የተከፋፈለ ማህበረሰብ ውስጥ የመደብ ወገንተኝነትን የሚያንፀባርቅ መያድ/ሚድያ በጎሳ ሽኩቻ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ላዕላይ መዋቅር በሰፈነበት ህብረተሰብ ውስጥ ያንኑ የሚያንፀባርቅ መያድም ሆነ ሚድያ መኖራቸው ብዙም ጥናት የማይጠይቅ እውነታ ነው። ይሁን እንጂ ምዕራባውያኑ በደፈናው የሚነግሩን ተፈጥሮአዊዲሞክራሲያዊነት ከመጠርያነት በዘለለ በተግባር ላይ ሲውል አናይም። በስርቆት ላይ ብቻ እንደተሰማሩ የሚታወቁም እንኳ ቢሆን፡መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዓይነተኛ መገለጫ በመሆናቸው ያሉትና ያረጉት ሁሉ በማንም ወገን ጥያቄ ውስጥ አይገባም። በሙስና ከሥልጣን የወረደ ሹመኛ በቀላሉ ሃጥያቱ እንዲሰረይለት ከፈለገ አቋራጩ መንገድ መያድ አቋቊሞስለ መልካም አስተዳደርልቡ ውልቅ እስኪል መታገል ብቻ ነው።

በምዕራቡ ዓለም ቡራኬ የማይገሠስ የሀቅ ሚዛንነት ሃላፊነትበ የተሰጣቸው ሌሎች ተቋማት ደግሞ የግል የመገናኛ ብዙሃን ናቸው። ጥላቻንና ሁከትን መስበክን ቋሚ አጀንዳቸው አድርገው የያዙትም እንኳ ቢሆኑ በምዕራባውያኑ መመዘኛ መሠረት የእውነት ሚዛኖች ሁነው መታየት አለባቸው። ጦርነት በመቀስቀሱና ከፍተኛ ወንጀል በመፈፀሙጋዜጠኛበህግ ቁጥጥር ስር የዋለ እንደሆነ፡ የዴሞክራሲ ሂደቱ እንደተቀለበሰ ሊቆጠር ይችላል። ባጭሩ የማተሚያ ቤት ወጪ ችሎነበልባል፣ማዕበል፣ቀረርቶ፣ሁከት…” የሚል ስም ጋዜጣውሰጥቶ የጭቃ ጅራፍ ሲያጮህ የሚውል ሁሉ ጋዜጠኛ ያሻውን የመፃፍመብቱየፕሬስ ነፃነት ህጉን ለማስከበር የተወሰደ ህጋዊ እርምጃ ደግሞ የፕሬስ ነፃነትን መዳፈር እንደሆነ በምዕራባውያኑ አስቀድሞ የተረጋገጠ ነው። ይኸን ዘመነኛ ቀኖና በትንሹም ቢሆን ለመፈተሽ የሞከረ መንግስትም ሆነ ሀገርከዴሞክራሲያዊ ሂደቱየማፈግፈግ አደገኛ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

እንደ ማጠቃለያ

ምዕራባውያኑ የዴሞክራሲ ስርዓት የማስፋፋት ተልዕኮአቸውን ለመወጣት የሚጠቀሙባቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ምዕራባውያን ተቋማት አሏቸው። የእነዚህ ተቋማት ዓላማ በአንድ ሀገር ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ በእጅጉ የተለየ ራሳቸውን የሚመች እውነታ መፍጠር ነው። ቢቢሲና ሲኤን ኤን፣ሁማን ራይትስ ዋችና ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢኒስትትዩት ወዘተርፈ ሁሉ የሂደቱ ዋነኛ መሣርያዎች ናቸው።የኢኮኖሚያዊ ተፅኖ መፍጠር የፈለጉባቸው ሀገራት ውስጥ ደግሞ ከላይ ለመጥቀስ የሞከርካቸው ሃይሎች አማራጭ እውነታ በመፍጠር ይተባበራቸዋል፡፡ እንግዲህ ይህን ለጥቅማቸው መረጋገጥ ሲባል ለሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት እንደ ግብዓት የሚያገለግል አማራጭ እውነታ የመፍጠርን ሂደት ነው ዴሞክራሲን የማስፋፋት ታሪካዊ ተልዕኮ በማለት የሚጠሩት፡፡

No comments:

Post a Comment