Pages

Wednesday, June 25, 2008

The Reporter Interview with Alemayehu Fentaw

In an interview with the Reporter, the Amharic private bi-weekly, Alemayehu Fentaw talks about federalism, democratization, and the role of political parties in the country as well as ethnic animosity in Ethiopian institutions of higher learning.

The Reporter
Wednesday, 16 January 2008
Addis Ababa

"መንግሥት ወታደሩ በመፈንቅለ መንግሥት ያስወግደው እንደሆነ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አሸንፈው ስልጣን አይዙም"
አቶ አለማየሁ ፋንታው

የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 8(1) "የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡" ማለቱ አንቀፅ 39(1) ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው" መባሉንና አንቀፅ 34(5) "የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሃይማኖቶች ወይም በባሕሎች ሕጎች መሠረት መዳኘትን አይከለከልም" መባሉ ህጋዊ መድብለ ብዙሃን ስርዓት ከፌዴራሊዝም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው ያሳያል፡፡

ሆኖም የፌዴራሉ መንግሥት በትክክል በሙሉ ሀይሉ የተዋቀረ ሲሆን ዘጠኙ የክልል መንግሥታት ግን ዛሬም ከ13 ዓመታት በኋላ እየተሰሩ ነው፡፡ አንቀፅ 50(5) "የክልል ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ስር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል ነው፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል ያፀድቃል ያሻሽላል፡፡" የሚል በመሆኑ ሁሉም ክልሎች ህገ መንግሥት አላቸው፡፡ ህገ መንግሥታቸው ከኢፌዲሪ ህገ መንግሥት ብዙም የተለየ ካለመሆኑም ባሻገር ክልሎች በህገ መንግሥት ትርጉም ያላቸውን ቀጥተኛ ያልሆነ ስልጣን ይቅርና በግልፅ የተቀመጠውንም ስልጣን ተግባራዊ እያደረጉት አይደለም፡፡ ፌዴራላዊ ስርዓት ከወረቀቱ ላይ እንዳለው በተግባር አያምርም፡፡ በኃይልስላሴ አስተዳደርና በወታደራዊው መንግሥት ላይ ይደርሱ የነበሩ ጫናዎችና የሕዝብ ጥያቄዎች በሕዝብ ተወካዮች ካውንስል አማካኝነት በረቀቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ረገብ ቢሉም አሁን በሕግ ማዕቀፉ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡

አቶ አለማየሁ ፋንታው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋኩልቲ አስተማሪ ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው የህግ መፅሄት ምክትል ዋና አዘጋጅ ናቸው፡፡ የህትመትና ምርምር ተቋሙ ተጠሪ ናቸው፡፡ በቅርቡ ለህትመት በበቃው መፅሄት በብሔር ብሔረሰቦች (ክልሎች) የህግ መድብለ ብዙሃን ስርዓት ግንባታ ላይ ጥናታዊ ፅሁፋቸውን አቅርበዋል፡፡ እኛም በዚህና በሌሎች የክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና በተግባር እየታዩ ስላሉ አንዳንድ ችግሮች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ህጉና ፖለቲካው በተጣጣመ መልኩ እየተጓዙ ነው? ብዙ አካሎች ጥርጣሬ አላቸው፡፡

አቶ አለማየሁ፡- የህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝሙን ስኬትና ውድቀት ለመመልከት ሁለት ነገሮችን ማዬት አለብን፡፡ በመጀመሪያ የህግ ማዕቀፉ ምን ይመስላል? የክልሎች ሚና ምንድን ነው? የፌዴራሉ ማዕከላዊ መንግሥት ያለው ሚና ምንድን ነው? የስልጣን ክፍፍሉ ምን ይመስላል? የገቢ ማሰባሰብ ክፍፍል ምን ይመስላል? ያለው የልማት አጋጣሚ ክፍፍል ምን ይመስላል? ለሚሉት ጥያቄዎች የህገ መንግሥቱ አንቀፆች ምን እንደሚል ከመመልከት ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ህገ መንግሥቱ እንዴት እየተተረጎመ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ለመጀመሪያው ጥያቄ የህግ መልስ ለሁለተኛው ጥያቄ የፖለቲካ መልስ ነው የሚያሻው፡፡ ህገ መንግሥቱ የፌዴራል ስርዓት እሴቶች ከመያዝ አኳያ አንኳር የሆነ ችግር የለበትም፡፡ ምናልባት አንዳንድ ግልፅ ያልሆኑና ያልጎሉ ነገሮችን ልናይ እንችላለን፡፡ ይህ ወደፊት የሚዳብር ነው የሚመስለኝ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግሥቱን በመተርጎም ሊሻሻል የሚችል ነው፡፡ የመገንጠል መብትን የያዘች አገር በዓለም ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ትሁን እንጂ ቀደም ብሎ ዩጎዝላቪያና ሶቭዬት ኅብረት በህገ መንግሥታቸው አካተውት ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው የመገንጠል መብትን ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ጋር አዳብላ በመያዟ ነው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ምን ያህል ውጤታማ ነው? በምንልበት ጊዜ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ናቸው በክልልም ሆነ በፌዴራል መንግሥት አብላጫ መቀመጫ ያላቸው እስካሁን፡፡ ስለዚህ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ የአንድ ፓርቲ ፍፁም አብላጫ የሚስተዋል በመሆኑና በፌዴራል ስርዓት አሀዳዊ የሚመስል የመአከላዊ መንግሥት እንቅስቃሴ የጎላበት ከመሆኑ አንፃር የህገ መንግሥቱ የ13 ዓመት ውድቀት ነው፡፡ የፌዴራል ስርዓቱን እንዲቀጥል የምናደርገው እንዴት ነው? ስርዓቱ አሀዳዊ ከመምሰል ወጥቶ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መቼ ነው በትክክል የሚሠራው? የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ካልዳበረና በዚሁ አሀዳዊ መሰል እንቅስቃሴ ከቀጠልን የፌዴራል ስርዓቱን ለማቆየትም እንቸገራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መዳበር ያደረጉት አስተዋፅኦ?

አቶ አለማየሁ፡- ዴሞክራሲ ከቆመባቸው መሠረታዊ አእማዶች አንዱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጐልበት ነው፡፡ ለዚህ ክፍት የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ደረቅ "እኔ አውቅልሀለሁ" የሚሉ ፓርቲዎች አያስፈልጉትም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካሄድ የፌዴራል ስርዓቱን ለመጠበቅና የብሔር ብሐረሰቦችንና የክልሎችን መብት የማስከበር ሂደቱን ከማፍጠን አልያም ከማጓተት አኳያ የሚጫወቱት ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ በሳል አመለካከትና አጀንዳ ሊይዙ ይገባል፡፡ ያለመታደል ሆኖ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣት የሚቆጠሩና አንዳንዴም የሉም የሚባልበት ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ብዙዎቹ እንደ ብርጭቆ ተሰባሪ ናቸው፡፡ አንድን ምርጫ እንኳን አይሻገሩም፡፡ ከመንግሥት ጫና ይልቅ ከራሳቸው በመነጨ ችግር ነው የሚከስሙት፡፡ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብና ክልል መብት እንዲጠበቅ አዳዲስና ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደራጀት፣ ያሉትም ራሳቸውን መፈተሽ መንግሥትም ያለጫና ተወዳድሮ የሚያሸንፍ መሆን አለበት፡፡ የአሜሪካ ህገ መንግሥት ፊላደልፊያ ላይ ሲፀድቅ ሙሉ አልነበረም፡፡ ህብረተሰቡ፣ ፍ/ቤቶች ፖለቲካ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች ናቸው በሂደት ያዳበሩት፡፡ በየጊዜው ወደ ኋላ ከመመለስ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያካተተውን ህገ መንግሥት ማስተካከያዎችንና ማሻሻያዎችን በማከል ዘላቂና ሁሉን የሚያስማማ በማድረግ ላይ ልናተኩር ይገባናል፡፡ ሁሌም ከዜሮ መጀመር ለእድገት ፀር ነው፡፡ የፖለቲካ ጨዋታ ህጉን በመከተል መከናወን አለበት፡፡ ህጎቹ የሚዳብሩበትን መንገድ በፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሃሳብ መለዋወጫ ፎረም ላይ በመሳተፍ ሁሉም የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የሕዝቡን አመለካከት በመቅረፅ በኩል አማራጭ የተጠኑ አሰራሮችን በማሳዬት መወትወትና ጫና ማሳደር መቻል አለባቸው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሆሆታ ከመፍጠር በቋሚነት ሕዝብን ማገልገልና አማራጭ መፍጠር መቻል አለባቸው፡፡ አለዚያ የፌዴራል ስርዓቱ ላይዘልቅ ሁሉ ይችላል፡፡ ምናልባት የፌዴራል መንግሥቱን ሲደክም ወታደሩ በመፈንቅለ መንግሥት ያስወግደው እንደሆነ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አሸንፈው ስልጣን አይዙም፡፡ እናም መልሰን ወደ አምባገነናዊ ስርዓት እንገባለን፡፡ ወታደሩ ደግሞ የብሔር ጥያቄን በአግባቡ ስለማይመልስ እርስ በርስ ተበላልቶ ኢትዮጵያ ትጠፋለች፡፡ ስለዚህ ራዕይና ተስፋ ሰንቀው መታገል አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ንቁ የህገ መንግሥት መተርጎም እንቅስቃሴ ተሳታፊ ባለመሆኑ መንግሥት እንደፈለገ ህገ መንግሥቱን እየተረጎመው እና ስልጣንን በማዕከላዊነት እያከማቸ ነው በማለት ይወቅሳሉ፡፡ የዳኝነት አካሉንና የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነትም በጥርጣሬ ነው የሚያዩት፡፡ ይህ አደገኛ አዝማሚያ በመሆኑ ችግሩ ምንድን ነው? መፍትሄውስ?

አቶ አለማየሁ፡- ህገ መንግሥቱ የዳኝነት አካሉም ሆነ የምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ እንደሆነ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙትና የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት ያፀደቀውን ቦርድ ነፃ አይደለም የምንለው ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ በመሆኑ ነው፡፡ ከመርህ አንፃር የተሳሳተ ነገር የለም፡፡ ተቃዋሚው ፓርቲ ሲያሸንፍ ያለ ችግር የሚሰራበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ተቋማዊና ግለሰባዊ ነፃነቱ በህግ ድጋፍ አለው፡፡ ለፖለቲካዊ ተግባራዊነቱ ሁላችንም ልንሰራበት ይገባል፡፡ ጥያቄው ገዥው ፓርቲ ያለውን የመንግሥት ተቋም በሙሉ የሚሽከረከር ነው፡፡ የዳኝነት አካሉንና ምርጫ ቦርድንስ ጫና ያደርግባቸዋል ወይ? የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊፈታ የሚችለው በህጉ ውስጥ መሻሻያ በማምጣት ሳይሆን ተወዳድሮ በማሸነፍ ተግባራዊ በማድረጉ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክልሎች የተሰጣቸውን ስልጣን የመጠቀም ችግር እንዳለባቸው በቅርቡ ባሳተሙት አንድ ጥናት ጠቁመዋል፡፡ ክልሎች ይህን ስልጣናቸውን የመጠየቅ ችግር የፌዴራል ማዕከላዊ መንግሥት ያን የሚያፋጥኑ የዴሞክራሲ ተቋሞችን ካለመመስረቱና ካለመስፋፋቱ ጋር እንዴት ይታያል?

አቶ አለማየሁ፡- የስልጣን ክፍፍሉን ስንመለከት ለክልሎች ለምሳሌ ህግ የማውጣት ስልጣንን ብንመለከት ህገ መንግሥቱ ቀላል የማይባል ስልጣን ሰጥቷል፡፡ ዋና ዋናዎቹ በርግጥ ለፌዴራሉ ማዕከላዊ መንግሥት ነው የተሰጡት፡፡ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 52 በግልፅ ከተዘረዘሩት የፌዴራል መንግሥት ስልጣን ውጭ የተቀሩት ለክልሎች እንደተተወ ይደነግጋል፡፡ ይህን ያልተወሰነ ሰፊ ስልጣን ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና የክልሎች መብት የሚጠበቀውም በሚፈጥሩት የራሳቸው ልዩ ቋንቋ፣ ባህልና ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ግምት ውስጥ የገባበት ህግ አውጭ፣ አስፈፃሚና ተርጓሚ አካል ሲኖራቸው ነው፡፡ ክልሎቹ እስካሁን የቤተሰብ ህግ ብቻ ነው ያወጡት፡፡ የወንጀል ህግ ማውጣት ይችላሉ ግን አላደረጉትም፡፡ እርግጥ የክልሎች ህገ መንግሥት አለ፡፡ በአሜሪካ ለምሳሌ የ3 ክልሎች ህገ መንግሥት የፌዴራሉን ህገ መንግሥት ይቀድማል፡፡ የክልል ህግ አውጭዎች ከራሳቸው ከሚመነጩ ጉዳዮች ላይ ስልጣን አላቸው፡፡ ከፌዴራል መንግሥቱም በላይ ለዜጎቻቸው መብት መስጠት ይችላሉ፡፡ መብትና ጥበቃዎቹ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ተመሳሳይ ናቸው ማለት ድግግሞሽ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ዝቅተኛውንና ከዚያ መውረድ የማይቻልበትን ስርዓት ነው የሚያስቀምጠው፡፡ የወንጀለኛ ህግ ስነ ስርዓት ህግ ማውጣት መብቱ እንዳላቸው በህገ መንግሥታዊ ትርጉም የተሰጠ ነው፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ስልጣናቸውን ያለመጠቀም ነገር አለ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየመሰረተና እያስፋፋ ያለው የዴሞክራሲ ተቋም ስልጣናቸውን እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ ብሔር ግጭት ለስልጣን ከሚደረግ ሽኩቻ ውጭ ሌላ መሠረት አለው? የእነዚሁ ብሔር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችስ ግጭት መንስኤው ምንድን ነው?

አቶ አለማየሁ፡- በአብዛኛው ፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚጀመረው ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ምክንያታዊ ያለመሆንና ግብታዊነት ያጠቃቸዋል፡፡ አብዛኛው ከስነ አመንክዶ ወጣ የማለት ነገር አለ፡፡ የ1960ዎቹን የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሁኜ አይቸው የነበሩትን ሁኔታዎች አሁን በማስተምርበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚነሳውን ግጭት በማይበት ጊዜ በአንፃራዊነት አሁን አገራዊ አጀንዳ አይደለም የሚያጋጫቸው፡፡ በውይይት የሚፈታ ትንሽ ችግር ነው ወደ ግጭት እየወሰዳቸው ያለው፡፡ በ1960ዎቹ እነዋለልኝ መኮንን ይጋጩበት የነበረው የመሬት ጥያቄ አይነት ነገር ዛሬ የለም፡፡ የማንነት ጥያቄም ሲነሳ አላየሁም የስርዓት ግንባታ ጥያቄ፣ (የህግ ማዕቀፍ"፣ የመሬት ጥያቄ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ይከበር ጥያቄ አሁን ተመልሷል፡፡ አዲስ ጥያቄ አላየሁም፡፡ አንድ ጥያቄ ማስታወስ ካለብኝ የፌዴራል ፖሊስ ካምፓስ መግባት የለበትም በማለት ያነሱት ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ተማሪው አዲስ ሀገራዊ አጀንዳ የሕዝብ ስሜት ሰምቶ እንደ በፊቱ መታገል ሳይሆን የሌላ ፓለቲካ ፓርቲ ወይም ውጫዊ አካል መጫወቻ ሲሆን ነው የምንመለከተው፡፡ በቅርቡ እንኳን በጅማና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተነሱት የብሔር ግጭቶች በህገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መፍትሔ ያልተሰጣቸው ጥያቄዎችን ያነሳ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ተማሪዎቹ ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት ላይ ጥያቄ ያነሱበት አጋጣሚ አለ፡፡ በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው ሁሉም ብሔሮች በእኩል አይን አይስተናጋዱም ይላሉ፡፡ የፌዴራል ስርዓቱንም ሕወሓት በበላይነት እየመራው ነው በማለት ተቃውሞ መነሳቱ በኦሮሞ አማራና ትግራይ ብሔርና ዜጎችን በጥርጣሬ እንዲተያዩ በር ከፍቷል፡፡ ይህን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?

አቶ አለማየሁ፡- የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያላቸው እርስ በርስ ግንኙነት እና ሁኔታ የአሻንጉሊት ገፅታ ያለው ነው የሚመስለው፡፡ በ1993 ዓ.ም ኢህአዴግ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባበት ዓመት ነበር፡፡ ያ ቀውስ አራቱ አባልና አምስቱ አጋር ክልሎች የራሳቸውን ህገ መንግሥት እንዲከልሱ አስችሏቸዋል፡፡ የሕወሓት የበላይነት ሊያሳስብ የሚገባው የፓርቲዎቹን አባላት እንጂ ሌላ ማንንም ሊሆን አይችልም፡፡ እየተጋጩ ያሉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የእነዚህ አባልና አጋር ድርጅቶች አባላት ከሆኑ ይህ ጉዳይ የሚነሳው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሀይማኖት ተፅዕኖ የፀዳ ነው፡፡ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ለማስተናገድ ዩኒቨርሲቲ አግባብ ያለው ቦታ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አማራውን የአለፈውን የበላይነቱን ለመመለስ እንደሚጥር፣ ኦሮሞውን መገንጠል የሚፈልገና በኢትዮጵያዊነት የማያምን፣ ትግራዩን ለገዥው ፓርቲ ፍላጎት ማርኪያ መሳሪያ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ እንዲሁም አንዱ ከሳሽ ሌላኛው ተከሳሽ መሆኑ አደገኛ አዝማሚያ ነው፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ በእንጭጩ እንዲገታ ምን መደረግ አለበት?

አቶ አለማየሁ፡- የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከማህበረሰቡ ሊቀድምና ማህበረሰቡን ሊያስተምር ለማህበረሰቡ መብትና ነፃነት መታገል የነበረበት ወገን ነው፡ አሁን የምናየው ግን ማህበረሰቡ ነው ተማሪውን ከፊት እየገፋው ያለው፡፡ የሚወደውና የሚግባባውን ጓደኛውን እንዴት ትናንት በታሪክ ተፈጥሮ በነበረ ጤናማ ያልሆነ የብሔር ግንኙነት የተነሳ ብሔሩን መዞ እጁን ይሰነዝርበታል? ይሄ ትግልም ትክክለኛ የዜግነት ስሜትም አይደለም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስሜታዊነት ያጠቃቸዋል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ መገንጠልም ቢሆን በህጉ ማዕቀፍ ውስጥ እስከተከናወነ ድረስ በእኛ ስርዓት መብት ነው፡፡ የትግራይ ተማሪም ከሌላው ብሔር ብሔረሰብ የተለዬ ጥቅም አያገኝም፡፡ ይህ የመቻቻል ፖለቲካ በሀገራችን ያለው ደረጃ ዝቅተኛ ከመሆኑ የመነጨ ነው፡፡ መንግሥት በተጠና መልኩ ይህን አደገኛ አዝማሚያ ለመግታት ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ይህ ግን መሠራት ያለበት ለጥናትና ምርምር በሚውሉት የዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ሳይሆን የፖለቲካ ቤተ ሙከራ በሚደረግባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ነው፡፡ ራሳቸው የገዥው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔር ፖለቲካን እንደ መድረሻ ሳይሆን እንደ ግብ ሊቆጥሩት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ህብረተሰቡስ በፌዴራል ስርዓቱ እድገት ላይ የሚጫወተው ሚና እንዴት ይታያል?

አቶ አለማየሁ፡- በግንቦት 97 ምርጫ እንደታየው ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የመምረጥ መብቱን በመጠቀም ትክክለኛው የስልጣን ባለቤት ሕዝብ እንደሆነ ሊያሳይ ይገባል፡፡ በተቃዋሚዎችም ሆነ በመንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰተው አሉታዊ ድርጊቶችን ሊያቃናቸው እንደሚችል ሊያስብ እንጅ ተስፋ ሊቆርጥ አይገባም፡፡ ሊያገኛቻው ሁሌ የሚሻቸው ሰላም ዴሞክራሲ ልማትና ነፃነት በመንግሥት ብቻ የሚሰጡ የሚሻሩ ትግል የሚደረግባቸውም በፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ እንደሆነ ሊያስብ አይገባም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ ብሎም ብሔርና ብሔረሰቦች በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሊታገሉ ህገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብት ማንም ሊሸርፍና ሊያስቀር እንደማይገባ ሊያምን ብሎም ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በባህል፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ተፅዕኖ የሚያደርጉ የሲቪክ ማህበረሰብ ሥራዎች ሊስፋፉና ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ያኔ ነው ፖለቲካ የ3 ወይም የ4 ሰዎች ጉዳይ ሳይሆን የሕዝብ ህልውና መሠረት የሚሆነው፡፡

http://www.ethiopianreporter.com/content/view/241/54/

No comments:

Post a Comment